ማልቀስ ጎጂ ነው ጠቃሚ

ሰዎች ካለቀሱ በኋላ ያስጨነቃቸው ነገር እንደሚቀላቸው የሚያስቡ ሲሆን በሰዎች ፊት ማልቀስ ደግሞ ደካማነት ተደርጎ ይታሰባል። ነገር ግን እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች ስህተት ናቸው ይላሉ በቅርቡ ጥናት የሰሩ ተመራማሪዎች።

ሊህ ሻርማን እና የምርምሩ ቡድን አባላት ይፋ ባደረጉት ውጤት መሰረት ሰዎች ካለቀሱ በኋላ ጥሩ ስሜት እንደሚሰማቸው ወይም አስጨናቂ ነገር አጋጥሟቸው በማልቀስ ነገሮችን ቀለል እንደሚያደርግላቸው ሊያምኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ማልቀስ እውነትም እንደዚህ አይነት ተጽእኖ ኖሮት ሳይሆን ስለማልቀስ ያላቸው አመለካከትና እምነት ነው። ወይም ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በሚኖርበት በማህበረሰብ ውስጥ ስለማልቀስ እየተነጋረ ያደግንበት ነገር ሁኔታውን የሚወስነው ይሆናል እንጂ፤ ማልቀስ በራሱ ምንም አይነት የሚፈጥረው ነገር የለም።

ሊህ ሻርማን እና ቡድኗ ሰዎች ስለማልቀስ ያላቸውን አመለካከት መለካት የሚችል ሙከራ ካዘጋጁ በኋላ ለፈቃደኛ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን አቅርበዋል። የመጀመሪያዎቹ ጥያቄዎች ስለማልቀስ ምን አይነት እምነት እንዳላቸውና በሰዎች ፊት ሲያለቅሱ ምን እንደሚሰማቸው ነበር የተጠየቁት። የምርምሩ ተሳታፊዎች ለዚህ ጥያቄ በሰጡት መልስ ላይ ተመስርተው ተጨማሪ 40 ጥያቄዎችን አዘጋጅተዋል። ያገኟቸውም ምላሾች ካለቀስኩ በኋላ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል ከሚሉት በሰዎች መሀል ሳለቅስ ተጋላጭነት/ደካማነት ይሰማኛል እስከሚሉት ድረስ ነበሩ።

ሊህ ሻርማን እና ቡድኗ ከፈቃደኛ የምርምሩ ተሳታፊዎች ካገኙት ምላሽ በመነሳት ስለማልቀስ ሦስት አይነት አስተሳሰቦች እንዳሉ ደርሰንበታል ይላሉ። እነሱም የሚከተሉት ናቸው

  • • ለብቻ ማልቀስ ጠቃሚ ነው፡ በዚህ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ሰዎች ነገሮች ሲያስጨንቁኝ ማልቀስ እወዳለሁ፤ ካለቀስኩኝም በኋላ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል የሚሉ ናቸው።
  • • ለብቻ ማልቀስ ምንም አይጠቅምም፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ በሆነ ነገር ተጨንቄ ለብቻዬ ካለቀስኩኝ እንደውም ይብስብኛል ያሉ ሲሆን አብረዋቸው ሰዎች ቢኖሩ ይመርጣሉ።
  • • በሰዎች መካከል ማልቀስ ምንም አይጠቅምም፡ ለተመራማሪዎቹ ይህንን ምላሽ የሰጡት ተሳታፊዎች በሰዎች መካከል ወይም ቤተሰብ ባለበት ቦታ ሳለቅስ የበታችነትና የመዋረድ ስሜት ይሰማኛል፤ የሚታዘቡኝም ይመስለኛል ያሉም ነበሩ።

አሜሪካዊው የሥነ አእምሮ ባለሙያ ራንዶልፍ ኮርኔሊየስ እ.አ.አ. ከ1885 ጀምሮ ላለፉት 140 ዓመታት የታተሙ ታዋቂ 72 የምርምር ውጤቶችን ጠቅሶ ባሰፈረው መረጃ መሰረት 94 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካዊያን ማልቀስ ለጤና ጠቃሚ ነገር እንደሆነ ያስባሉ። ነገር ግን የዘርፉ ተመራማሪዎች አገኘነው በሚሉት መሰረት ማልቀስ ተቃራኒ የሆነ ተጽእኖ ነው ያለው። ሰዎች ካለቀሱ በኋላ ከጥሩ ስሜት ይልቅ እንደውም የባሰ ደስ የማይል ስሜት ውስጥ እንደሚገቡ ያሳያል።

እ.አ.አ. በ2016 የተሰራ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ማልቀስ የሚያበዙ ሰዎች ከማያለቅሱ ሰዎች አንጻር ደካማና ተወዳዳሪ ያልሆኑ ተደርገው ይወሰዳሉ። በተጨማሪም ማልቀስ የሚያበዙ ወንዶች ከሴቶች በባሰ መልኩ እንደ ደካማ እንደሚቆጠሩም ጥናቱ ያሳያል።

በዚህም መሰረት ሰዎች ከሥራ ቦታ ይልቅ ቤተሰብና ጓደኞቻቸው ፊት ማልቀስን የሚመርጡ ሲሆን፤ ወንዶች ደግሞ በየትኛውም ሁኔታ ሲያለቅሱ ላለመታየት ይጥራሉ። በሌላ መልኩ ደግሞ በሥራ አካባቢ ማልቀስን የሚያዘወትሩ ሴቶች የሚፈልጉትን ነገር ሰዎች እንዲፈጽሙላቸው ለማስገደጃነት እንደሚጠቀሙበት ጥናቱ መረጃ አለኝ ይላል።

በሥራ ቦታም ሆነ በሌሎች የማህበራዊ ሁነቶች ላይ የሚያለቅሱ ሴቶች እንደ ደካማ ከመቆጠራቸው በተጨማሪ ነገሮች ሲያስጨንቋቸው ከሚያለቅሱ ወንዶችም ጭምር እንደሚያንሱ ይታሰባል። ይህ ደግሞ ከማልቀስ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን ለሴቶች ካለው የተሳሳተ አመለካከት ጋር የሚያያዝም ነው። ሊህ ሻርማን ደግሞ፤ ሰዎች ካለቀሱ በኋላ በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎች ጥሩ ስሜት እንደሚሰማቸው ስለሚገምቱ ከእነሱ ጋር ለመመሳሰል ሲሉ መጥፎ ስሜት ላይ ቢሆኑ እንኳን ደህና እንደሆኑ ይናገራሉ፤ ለእራሳቸውም ይህንኑ ነው የሚነግሩት። በዚህም መሰረት የሊህ ሻርማን እና የጥናት ቡድኗ ሰዎች ስለማልቀስ ያላቸው አመለካከትና የሚሰማቸው ስሜት እንደ አካባቢው ባህልና አረዳድ የሚወሰን ሲሆን ማልቀስ በራሱ ግን ምንም አይነት ነገሮችን ቀለል የማድረግ ተጽእኖ የለውም ይላሉ።