ስራን ከልክ በላይ የመደጋገምና የማረጋገጥና ባህሪ – ኦሲዲ

ምሥራቅ* ለዚህ ታሪክ ሲባል ስሟ የተቀየረ “ለሦስት ዓመታት የማስበውን ሁሉ እንድጽፍ አእምሮዬ ያስገድደኝ ነበር” ትላለች። እንቅልፍ እና እርሷ ተፋትተው ነበር የከረሙት። “ዝም ብዬ መጻፍ ነው። ደብተር፣ ወረቀት፣ ሞባይል ሁሉ ነገር ላይ እጽፋለሁ።” የምትጽፈው ነገር ለሚያነበው ሰው ትርጉም ላይሰጥ ይችላል። ማንኛውንም ነገር በአእምሮዋ ውስጥ ሰንዳ የያዘቸውን ወይም የመጣላትን ጥቃቅን ነገር ሁሉ ካልጻፈች ሰላም ይነሳታል። “ፀጉሬ ላይ ቅባት ተቀብቼ ጥሩ ነው ብዬ ካሰብኩኝ እጽፈዋለሁ።” ይህ የመጻፍ ጉትጎታ ግን አንድ ቀን ተገታ። “አንድ ቀን ለሊቱን ሙሉ ቁጭ ብዬ ስጽፍ አደርኩ፤ የዚያን ቀን ይህ ነገር የወጣልኝ ይመስለኛል።” ምሥራቅ ባይፖላር ዲስኦርደር በተባለ የአእምሮ ሕመም (በሁለት የተለያዩ የስሜት ጽንፎች መካከል መዋለል) እየተቸገረች እያለ ነው ይህ ዕክል የተጨመረባት። ኦሲዲ (ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር) ይባላል ነገሮችን በተደጋጋሚ ለመስራት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ጎትጓች ስሜት መሰማት ነው። “በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፤ አሁን በሕይወት መኖሬ በጣም ይገርመኛል፤ ሥራዬን ለቅቄ ነበር። ይህንን በራሴ መቆጣጠር ስላቃተኝ መልሶ ጭንቀት ውስጥ አስገብቶኛል። ”ምሥራቅ ሕመሟን ለሌሎች መንገር አልፈለገችም። ምክንያቷ ደግሞ ‘ማን ይረዳኛል’ የሚል ነበር። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ ይህ ሕመሟ እንደ አዲስ ተመልሶ አገረሸባት። “የዘጋሁትን በር እንዳልዘጋሁ ይሰማኛል። በተለይ ደግሞ የእሳት ነገር ወደ ጭንቅላቴ እየመጣ ያስጨንቀኛል፤ ስቶቭ ለኩሼ የተውኩ ያህል ይሰማኛል። በዚህ ምክንያት ቀኑን ሙሉ ስብሰለሰል ነው የምውለው።” ምሥራቅ አእምሮ ውስጥ እየመጣ የሚያስጨንቃት ጎትጓች ሃሳብ፣ ሕመም መሆኑን ሳታውቅ ለረዥም ጊዜ ቆይታለች። ይህ ጉዳይ ሕመም እንደሆነ ያወቀችው በቴሌቪዥን ካገኘችው መረጃ የተነሳ ነው። ቢቢሲ ወደ ሕክምና አልሄድሽም ሲል ጠይቋት ነበር። “ሕክምና ለማግኘት ስሄድ አእምሮሽን ዝም አስብይው ይሉኛል። ግን እርሱን ማድረግ ብችል ኖሮ ለምን ወደ ሕክምና እሄዳለሁ” ትላለች።

ባለሙያዎች ስለ ኦሲዲ ምን ይላሉ?

ሐኪም የተሰኘው እና በሕክምና ባለሙያዎች የተመሰረተው ማኅበራዊ ድረ ገጽ ኦሲዲ (ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር)ን በተመለከተ ይህንን ይላል። “ኦሲዲ በአጭሩ ሲገለጽ ጥርጣሬ የሚፈጥር የሚነዘንዝ ሀሳብና እና ሃሳብ ተከትሎ ለማርገብ የሚደረግ ተደጋጋሚ ድርጊት ነው” ሲል አስፍሯል። በዚህ የአእምሮ ሕመም ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሕመሙ በየትኛውም የእድሜ ክልል ያለ ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል። የህመሙ መንስዔ ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም። ዶክተር ዮናስ ባሕረጥበብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአእምሮ ሕክምና ክፍል መምህር ሲሆኑ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደግሞ የአእምሮ ሕመም ሐኪም ናቸው። ሐኪሙ ይህንን ሕመም ሲገልፁት “ከእኛ ፍላጎት ውጪ፣ ወደ አእምሯችን የሚመጣ ሐሳብ ወይንም ደግሞ አንድን ድርጊት በተደጋጋሚ ለመፈፀም መፈለግ፣ በተግባርም ማዋልንም ይጨምራል” ይላሉ። ዶ/ር ዮናስ እንደሚሉት በዚህ የአእምሮ ሕመም የተያዙ ሰዎች ወደ አእምሯቸው የሚመጣውን ሐሳብ መቆጣጠር ካለመቻላቸው በተጨማሪ ያለፍላጎታቸው ወደ ጭንቅላታቸው የሚመጣ ነው። “በተጨማሪም ይህ ያለፍላጎታችን የሚመጣብን ሐሳብ ደስ የማይል እና የሚያስጨንቀን ሊሆን ይችላል” ሲሉ ያክላሉ። በልጅነታቸው ሥነ ልቦናዊም ሆነ አካላዊ ጥቃት ወይንም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሲጎለምሱ ለዚህ ሕመም ሊጋለጡ እንደሚችሉ ይናገራሉ። “አንዳንድ ሰዎች ወደ አእምሯቸው የሚመጣ ተደጋጋሚ ሃሳብ ብቻ ሊኖራቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ አንድን ነገር ደጋግሞ የመፈፀም ጠንካራ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል። ያንንም በመፈፀም ለአጭር ጊዜም ቢሆን እፎይታ ያገኙ ይመስላቸዋል” ይላሉ። ዶ/ር ዮናስ ይህንን በምሳሌ ሲያስረዱ፣ “አንድ ሰው በሃሳቡ እጅህ ላይ ጀርም ወይንም ደግሞ እጅህ ቆሻሻ ነው የሚል ነገር ይመጣበታል። ይህም አንዴ እና ሁለቴ ሳይሆን በተደጋጋሚ ስለሚመጣበት እጁን ንፁህ እንደሆነ ቢያውቅ እንኳ በቀን እስከ 30 ጊዜ ሊታጠብ ይችላል።” “ደምህ ውሰጥ ኤችአይቪ አለ የሚል ሃሳብ የሚመጣባቸው ሰዎች አሉ። ያ ሰው ተመርምሮ በሽታው በደሙ ውስጥ እንደሌለ ቢያውቅ እንኳ ይህንን ተደጋጋሚ ሀሳብ ግን ማቆምም ሆነ ማቋረጥ አይችልም።” ዶ/ር ዮናስ እንደሚሉት ይህ ኦሲዲ የተባለ የአእምሮ ሕመም ሥራ እየሰራን ወይንም በየትኛውም የሕይወታችን እንቅስቃሴ፣ በመካከል ሊመጣብን ስለሚችል የምንሰራውን ወይንም ድርጊታችንን አቁመን በሃሳቡ ልንያዝ እንችላለን። “እኛ የማንፈልገው፣ ፈጣሪያችን የሚያሳዝን ሃሳብ ወደ አእምሯችን ይመጣል፤ ማስቆም አልቻልንም ብለው ለሕክምና ወደ እኛ ይመጣሉ” ሲሉ ባለሙያው ከልምዳቸው ይናገራሉ።

ይህ ሁኔታ መቼ ወደ ሕመምነት ይቀየራል?

ዶ/ር ዮናስ ይህ ሁኔታ ሕክምና ሊያስፈልገው ደረጃ ላይ የሚደርስበት ዕድል ስላለ ምልክቶቹን መረዳት አስፈላጊ ነው ይላሉ።

  • አንድ ሰው የማይፈልገው ሃሳብ ወይንም ደግሞ ተደጋጋሚ ሃሳብ በቀን ከአንድ ሰዓት በላይ የሚመጣበት ከሆነ፣
  • እጅ መታጠብ እና መሰል ተግባራትን ከቁጥጥሩ ውጪ በሆነ ሁኔታ የሚያደርጋቸው ከሆነ፣
  • የዕለት ተዕለት ሥራውን በዚህ ምክንያት መፈፀም ካልቻለ እና ይህም የሚረብሽ ስሜት የሚያመጣ ከሆነ
  • ከቤተሰቡ እና ከጓደኞቹ ጋር ያለው ግንኙነት ከተዛባ
  • በተጨማሪም ይህ ተግባር እና ሃሳብ ሰላም የሚነሳ፣ ደስታ የሚያሳጣ ከሆነ ይህ ሰው እየታመመ ነው ማለት እንችላለን።

ከዚህ ውጪ ግን ይህ ሁኔታ እንደ ባህርይ ብቻ ያላቸው ሰዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሰሩ ይሆናሉ ይላሉ። “የሂሳብ ባለሙያዎች፣ በተደጋጋሚ የማጣራት እና የማረጋጋጥ ባሕርይ ስላላቸው ስሌት አይሳሳቱም። ሌሎች እንደ ፓይለት እና ሜካኒክ ዓይነት ሥራዎችም ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚፈልጉ ይህንን ዓይነት ባሕርይ ያላቸው ሰዎች በእነዚህ ሙያዎች ልህቀትን ሊያሳዩ ይችላሉ።” አክለውም ይህ የኦሲዲ ሕመም በራሱ ወደ ሌላ ከባድ የአእምሮ ሕመም ባይቀየርም፣ ነገር ግን ወደ አእምሯችን የሚመጣ ተደጋጋሚ ሃሳብ እና የምንፈጽመው ተደጋጋሚ ድርጊት መልሶ ሊያስጨንቀን ወይንም ደግሞ ድባቴ ሊያመጣ እንደሚችል ዶ/ር ዮናስ ይገልጻሉ። ለዚህ ሕመም የሚሰጠው ሕክምና በቂ አለመሆኑን የምታስረዳው ምሥራቅ፣ “በሩን ክፍቱን አድርጌ ብሔድ፣ ሊፈጠር የሚችለው ክፉ ነገር ምን ሊሆን ይችላል ብዬ በማሰብ፣ ሃሳቡን ለማስቆም እጥር ነበር። ነገር ግን መጨረሻ ላይ ስላልቻልኩኝ መድኃኒት መውሰድ ግድ ሆነ” ትላለች። አሁን በፀሎት እና በተሰጠኝ መድኃኒት ለውጥ እያሳየሁ ነው ስትል የምትናገረው ምሥራቅ፣ ለሕመሟ የተሰጣት መድኃኒት መጀመሪያ አካባቢ ሕመሟን አብሶባት እንደነበር ታስታውሳለች። “በዚህ ምክንያት መድኃኒቱን ከሁለት ጊዜ በላይ ቀይሬያለሁ።” በዚህ ሕመም ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚሰጣቸው የተለያየ ዓይነት ሕክምና አለ። አንዱ የሥነ ልቦና የምክር አገልግሎት ሲሆን በዚህም ሳይፈልጉት የሚመጣባቸውን ሃሳብ ሊቆጣጠሩ የሚችሉበትን ዘዴዎች ይማራሉ። ሁለተኛው ደግሞ አእምሮ እና ሰውነት እንዲፍታታ የማድረግ ሕክምና ነው። “ለምሳሌ ሜዲቴሽን (አርምሞ)፣ እንደ ዮጋ ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ማሳጅ ማድረግ” ናቸው። ከእነዚህ ባሻገር ደግሞ በሽታውን ሊቆጣጠረው የሚችለው መፍትሔ ለሕመሙ የተዘጋጀውን መድኃኒት መውሰድ ነው። እነዚህ የሕክምና ዓይነቶች የሰውየው የሕመም ዓይነት እና ደረጃ ላይ በመመስረት ከበሽታው እንዲድን ሊያደርጉ ይችላሉ ይላሉ ዶ/ር ዮናስ። አሁን እየተሻላት እንደሆነ የምትናገረው ምሥራቅ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ምልክቶችን ካዩ በፍጥነት ወደ ሕክምና እንዲሄዱ ትመክራለች።