በሁለት የስሜት ጽንፍ ውስጥ መዋለል- ባይፖላር ዲስኦርደር

እሌኒ ምስጋናው በአስራዎቹ የእድሜ ክልል እያለች ባሕር ማዶ ሄዶ የመማር እድል ገጠማት። አጎቷ የሚኖረው አውሮፓ ነው። ከቤተሰብ መካከል አንድ ልጅ ወስዶ ለማስተማር እንደሚፈልግ ሲናገር እሌኒ ተመረጠች። ወዳጅ ዘመድ በጉጉት ይጠብቀው የነበረው ዕድል ነው። “ገና የስምንተኛ ክፍል ፈተናን ሳልወስድ ነው ወደዚያ ያመራሁት። ገና ልጅ መሆኔ ብቻ ሳይሆን፣ አገሬው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ መሆኑ ቆይታዬን አከበደው” ትላለች ሁኔታውን መለስ ብላ ስታስታውስ። አራት ዓመት ድረስ ጥሩ ተማረች። እሌኒ፣ ቤተሰቦቿም ሆኑ እርሷ ሃይማኖታቸውን አጥባቂ መሆናቸውን ትናገራለች። በእርሷ አገላለጽ “ወግ አጥባቂ” የሚባሉ ዓይነት ናቸው። አጎቷ የውጭ አገር ዜጋ አግብቶ የሚኖር እና ኢአማኒ ‘ኤቲይስት’ በመሆኑ የእሌኒን ጫና የበለጠ አበረታው። ይህ የባህል መጣረስ የእሌኒን የልጅነት አእምሮ ክፉኛ ተጫነው። በአንድ ወገን ትምህርት በሌላ በኩል የባህል ልዩነቱ ብርቱ ክንዳቸውን አሳርፈው ልጅነቷን ተጫኑት። እነዚህ ሁሉ ተደራርበው ታመመች። ሕመሟ ሆስፒታል እንድትገባ አደረጋት። ከሆስፒታል ግን ለመውጣት ሦስት ወር ፈጀባት። እናቷ ከአዲስ አበባ ተጠርተው ያለችበት ድረስ ሄዱ። ገና አፍላ ጎረምሳ እያለች፣ 18 እና 19 ዓመቷ ላይ የ’ባይፖላር ዲስኦርደር’ ታማሚ መሆኗን አወቀች። የጤና ሁኔታዋ ባሕር ማዶ ቆይታ ትምህርቷን እንድትቀጥል አላስቻላትም፤ ወደ አዲስ አበባ ከእናቷ ጋር ለመመለስ ተገደደች። ከዚያም ትምህርቷን አቋርጣ፣ ሕክምናዋን ስትከታተል ለአንድ ዓመት ቆየች።

“በወቅቱ የውጭ ዕድል አግኝቶ መሄድ ሎተሪ እንደማሸነፍ የሚቆጠርበት ወቅት ነበር። ያንን ዕድል አግኝቶ፣ የአእምሮ ሕመምተኛ ሆኖ መመለስ ጫናው ቀላል አልነበረም። ለእኔም ለቤተሰቤም ትልቅ ውድቀት ነው ብዬ ነበር የማስበው” ትላለች። እርሷ ብቻም ሳትሆን በዙሪያዋ ያሉ ሰዎችም አስተያየት ይሰጣሉ። አንዳንድ የቤተሰብ አባላት ‘ምነው ዕድሉ ለእኔ በተሰጠኝ ኖሮ’ ሲሉ ትሰማለች። እሌኒ ያንን የውጭ ዕድል አግኝታ ሳትጠቀም እንደ ቀረች ሰው በዙሪያዋ ባሉ ሰዎች መታየቷ ጫናዋን አከበደው። “አንድ ዓመት መድኃኒት እስኪለምድልኝ እና እስክረጋጋ ድረስ ከትምህርት ገበታ ርቄ ቆየሁ።” ከዓመት በኋላ ግን ወደ ትምህርት ቤት ተመለሰች። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ስትወስድም ዩኒቨርስቲ የሚያስገባትን ነጥብ አመጣች። የዩኒቨርስቲ ቆይታዋም ቢሆን ውጣ ውረድ የበዛበት ነበር። በፈተና ወቅት ያለው መጨናነቅ ሕመሟን ዳግም ስለሚቀሰቅሰው ትወስድ የነበረው መድኃኒት ይለወጥላታል። አንዳንዴ እንቅልፍ ይከዳታል። የመድኃኒት እጥረት ተፈጥሮ መድኃኒት ሲቀየርላት ሕመሟ ዳግም ይቀሰቀሳል። በክፍል ውስጥ የተሰጣትን መልመጃ ለማቅረብ ስትዘጋጅ ልቧም እግሯም ይርዳሉ። ሕመሙ ያገረሽባታል። “በመሃል ደግሞ ሕመሙ ይነሳብኛል። ከሕመሙ ጋር በደንብ አልተዋወቅንም ነበር።” የሕክምና ባለሙያዎች ምክር፣ የቤተሰቦቿ ድጋፍ እንዲሁም የምትወስደው መድኃኒት ረድተዋት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያዘች። “ባንክ ተቀጥሬ ስሰራ ቆየሁኝ። በኋላ ግን የፋይናንስ ሴክተሩ ጥሪዬ አለመሆኑን ስረዳ ሶሲዮሎጂ አጥንቼ ሙያዬን ቀየርኩ።” በዚህ ሂደት ውስጥም ከሕመሙ ጋር እየተላመደች መጣች።

ሕመሙ ሁለት ጽንፎች አሉት። አንደኛው ጽንፍ የድብታ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የተትረፈረፈ ደስታ፣ የስሜት ትፍስህት የሚጎርፍበት ነው።

ባይፖላር ዲስኦርደር ምንድን ነው?

ባይፖላር ዲስኦርደር የስሜት መዋዠቅ ነው። ሕመሙ ሁለት ጽንፎች አሉት። አንደኛው ጽንፍ የድብታ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የተትረፈረፈ ደስታ፣ የስሜት ትፍስህት የሚጎርፍበት ነው። በዚህ በሽታ የተያዘ ማንኛውም ሰው በሁለቱ ጽንፎች መካከል ይዋልላል። ድብታው ሲጫነው ከዚያ ለመውጣት መድኃኒት ይሰጠዋል። ይህ መድኃኒት ደግሞ ከእውነታው ዓለም ወደ ተፋታ ስሜት እንዳያስገባው ሌላ መድኃኒት ጨምሮ መውሰድ ይኖርበታል። እሌኒም ለዚያ ነው የተለያዩ መድኃኒቶች ቅንብር እንደምትወስድ የምትናገረው። በድባቴ ውስጥ የሚሆን ሰው ነገሮችን በአሉታዊ ጎኑ ብቻ መመልከት፣ መንቀሳቀስ እና መስራት አለመቻል፣ አቅም እና እንቅልፍ ማጣት፣ የምግብ ፍላጎት አለመኖር፣ አቅም ኖሮት ቢሆን እንኳ መንቀሳቀስ አለመቻል  መገለጫዎቹ ናቸው። ሌላኛው ጽንፍ ደግሞ ‘ማኒክ’ (manic) የሚባለው ነው። በዚህ የስሜት ጽንፍ የሚንገላታ ግለሰብ በጣም ኃይለኛ ጉልበት ይኖረዋል። እንቅልፍ አይተኛም። ራስን በጣም ከፍ አድርጎ መመልከት ይኖራል። እሌኒ ይህ ስሜት ውስጥ ስትሆን የሚሰማትን ስታስረዳ “ራሴን ከፈጣሪ አንድ ልዩ ተልዕኮ አንደተሰጠው ሰው አድርጌ እቆጥራለሁ። በጣም የተትረፈረፈ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል። ከሰው ጋር ለመነጋገር፣ ለመወያየት አቅም ይኖረኛል” ትላለች። ሌላ ጊዜ ለመስራት የማትደፍረውን በዚያ ወቅት ለመስራት እንደምትደፍር፣ ገንዘብ በጣም እንደምታባክንም ትናገራለች። “ሁሌ ለሁሉ ሰው መስጠት ነው.  . . አንድ ጊዜ የተትረፈረፈ ደስታ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የድብታ ሸለቆ ውስጥ የመግባት ስሜት ይሰማኛል።” በዚሁ በሁለት የስሜት ደርዞች ውስጥ ለሚዋልል ሰው የሚሰጡት የመድኃኒት ቅንብር የሚረዱት ያሉበትን ስሜት ለማስተካከል ነው። “ሁሉንም ዓይነት ስሜቶች አስተናግጃለሁ፤ እኔ ጋር ብዙ ጊዜ የሚታየው ድብታው ነው” የምትለው እሌኒ ድብታ ውስጥ ስትሆን ሥራ መስራት አለመቻል፣ ትኩረት ማጣት ይፈትኗት እንደነበር ትናገራለች። ካለችበት የስሜት ጽንፍ ለመውጣት ከሚሰጣት መድኃኒት ባሻገር የሕክምና ባለሙያዎች ምክር  እንድትረጋጋ እንደሚረዳት ገልጻለች።

ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል?

ባይፖላር ዲስኦርደር በምን ምክንያት እንደሚከሰት እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል የተረጋገጠ ምክንያት የለም። ነገር ግን ከቤተሰብ መካከል በዚህ ሕመም ያጋጠመው ሰው ካለ፣ ሌሎች የቤተሰብ አባላት ላይ የማጋጠም ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለበርካታ ሰዎች ችግሩ የሚቀሰቀሰው በእድሜ ከፍ ካሉ በኋላ ቢሆንም፣ እንደ እሌኒም በአፍላ እድሜያቸው ላይ ያሉ ሰዎች ላይም ሊከሰት ይችላል። በአፍላዎቹ እድሜ በዚህ የስሜት መዋዠቅ የአእምሮ ጤና ችግር ለሚያጋጥማቸው ሰዎች ምክንያት ሊሆን ከሚችሉ ነገሮች መካከል፤ የሕይወት መስመር በድንገት መቀየር፣ በተለያየ ምክንያት ከቤተሰብ ርቆ መሄድ እንዲሁም የሚወዱትን ሰው ማጣት ሊሆኑ ይችላሉ።

‘ምልክቶቹን ለምጃቸዋለሁ’

እሌኒ እንደምታስረዳው ባይፖላር ዲስኦርደር ያለበት ሰው ላይ የሚታዩት የሁለቱም ጽንፎች ምልክቶች አሉት። ከሕመሙ ጋር ረዥም ጊዜ በመቆየቷ ምልክቶቹን ቀድሞ የማወቅ ልምድ አዳብራለች። “ወደ ድባቴ ውስጥ የምገባ ሲመስለኝ በጣም እንቅልፍ እተኛለሁ። ቶሎ ቶሎ ስሜቴ ይለዋወጣል። ሌላ ጊዜ ማድረግ የሚያስደስተኝን ነገር ስሜት አጣበታለሁ። እንደዚህ ዓይነት ስሜቶች ሲኖሩ ወደ ድባቴ እየገባሁ እንደሆነ እገምታለሁ።” እርሷ ብቻ ሳትሆን ቤተሰቦቿም እነዚያን ምልክቶች ካዩ መድኃኒት መውሰዷን ይጠይቃሉ። “ትንሽ ስሜት ለውጥ ራሴ ላይ ስመለከት ቶሎ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ መድኃኒቶቹ እንዲስተካከል ይረዱኛል። የምክር አገልግሎት ይሰጠኛል” ትላለች። “ሌላኛው ጽንፍ ደግሞ እንቅልፍ ሳልተኛ ስቀር፣ አእምሮዬ በጣም ከሚገባው በላይ ንቁ ሲሆን፣ ሌላ ጊዜ የማልደፍረውን ሰው በድፍረት መናገር ስጀምር፣ ገንዘብ አያያዝ ላይ ከዚህ በፊት የማላደርገውን ዝም ብዬ ሳደርግ፣ ቶሎ ወደ ሃኪም ቤት እሄዳለሁ።” ባይፖላር ህመም ከምንም በላይ ራስን መግራት፣ ራስን በሥርዓት መምራት ይጠይቃል ትላለች እሌኒ። “ምክንያቱም የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት የሕይወት ዘይቤን ማስተካከል ይጠይቃል። ብዙ ደስታዎች ያሉበት ቦታ ወይንም ደግሞ ይህንን ስሜት የሚቀሰቅሱ ቦታዎች ላይ መቆየት የለብኝም።” “ወደ ተትረፈረፈ ደስታ እየሄድኩ ከሆነ መቀነስ ያለብኝ የማኅበረሰብ ግንኙነቶች ይኖራሉ። ራሴን ገታ ማድረግ ይኖርብኛል።”

 የመድኃኒት ቅንብር

እሌኒ ከስድስት ወር በፊት ሥራ መስራት፣ ትኩረት ማድረግ እንዳቃታት ታስታውሳለች።

“ደስታ አጣሁ፣ እንቅልፍ ሌሊት አይወስደኝም። ተኝቼ ጠዋት ስነቃ በሚገባ አልነቃቃም። እንቅልፍ ብተኛም የተኛሁ ያህል እርፍ ብዬ አልነሳም። አልቅሽ አልቅሽ ይለኛል” ትላለች የነበረችበትን ሁኔታ ስታስታውስ። ያኔ የገባችበትን ድብታ የሚቀንስ መድኃኒት ተሰጣት። “ይህንን መድኃኒት ደግሞ በሚገባ ካልተቆጣጠርነው ወደ ማይፈለገው እና ወደ ተትረፈረፈ ደስታ መውሰድ አቅም አለው። ስለዚህ አብሮ ያንን ገታ የሚያደርግ መድኃኒት መውሰድ አለብኝ።” ምንጊዜም ድብታ ውስጥ ስትገባ የሚሰጣት መድኃኒት፣ ከእውነታው ዓለም ወደ ሚቃረን ሁኔታ ውስጥ እንዳያስገባት ሌላ መድኃኒት አብራ እንድትወስድ ይደረጋል። “በተጨማሪ ሙድ ስታቢላይዘር [ስሜትን የሚያረጋጉ] እወስዳለሁ” ትላለች። እነዚህን መድኃኒቶች በአንድ ላይ መውሰድ ከባድ መሆኑን የምትናገረው እሌኒ፣ አንዳንዴ የትኛውን መድኃኒት መውሰድ እንዳለባ መለየት እና እርሱን መጠቀም እንደሚጠይቅ ታስረዳለች። ከእርሷ ጋር የሚስማማ መድኃኒት እስኪገኝ ድረስ ሌላ መሞከርም እንደሚኖርም አልሸሸገችም። “የጎንዮሽ ጉዳት ይኖረውና መቀየርም ይኖራል” ትላለች። በዚህ ጊዜ ሁሉ የስሜት መዋዠቅ እንደሚያጋጥም እና የተስተካከለ ነገር ላይ እስኪደረስ እንደሚያስቸግር ትገልጻለች። “የተስማማኝ ሙድ ስታብላይዘር ከአገር ውስጥ ሲጠፋ ደግሞ ሌላ መድኃኒት መቀየር ይጠይቃል። ያኔ ደግሞ የስሜት መዋዠቅ ይከሰታል።” አንድ መድኃኒት ከቅንብሩ መጉደል ወይንም መቀየር የስሜት መዋዠቅ፣ ከድብታ ወደ ተትረፈረፈ ደስታ ይጥላል።

የቤተሰብ ድጋፍ

እሌኒ የጤንነት ሁኔታዋ ባላወላዳ ጊዜ ሁሉ ቤተሰቦቿ ከጎኗ መሆናቸውን ትናገራለች። በተለይ አግብቼ ለሦስት ዓመት ያህል ምንም ዓይነት ሕመም አልነበረኝም ስትል ትመሰክራለች። ቤተሰቦቿ የስሜት መዋዠቅ ሲኖር ቀድመው ስለሚያውቁ፣ ሕክምና ድጋፍ እንድታገኝ ያስታውሷታል፣ መድኃኒቷን እየወሰደች መሆኑን ያረጋግጣሉ። “ከነበረው ባሕሪ ውጪ የሆኑ ነገሮች ሲሆኑ የበለጠ የሚታወቀው ለውጪ ሰው ነው።” በተለይ ሕሙማን ከእውነታው ዓለም የራቀ ስሜት ውስጥ በሚገቡበት ወቅት፣ አንዳንዴ ድምጽ መስማት፣ ለብቻ መነጋገር ይኖራል። ይህንን የሚለየው ቤተሰብ ነው። ድብታ ከሆነ ግን በአብዛኛው ሕመምተኛ ግለሰቡ ራሱ ያውቀዋል። ባይፖላር ችግር ያለበት ሰው ያለጭቅጭቅ፣ ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖር ማድረግ ወሳኝ ነው። በዚህም “እኔ በጣም ተጠቅሜያለሁ፤ ካገባሁ በኋላ ሦስት ዓመት ሙሉ ያለምንም ምልክት ነው የኖርኩት” በማለት የቤተሰብ ድጋፍ አስፈላጊነትን ትናገራለች።

ሌሎችን ለመደገፍ የመሰረተችው ማኅበር

እሌኒ ምስጋናው ለረዥም ዓመታት የአእምሮ ጤና ሕክምና ስትከታተል ከቆየች በኋላ፣ ከሌሎች አራት ጓደኞቿ ጋር በመሆን፣ የአእምሮ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማኅበርን መስርታለች። ማኅበሩ የአእምሮ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች በመደበኛ አባልነት ይዟል። የታማሚ ቤተሰቦች ደግሞ የክብር አባል መሆን ይችላሉ ትላለች። እነዚህ የተለያዩ የአእምሮ ጤና ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች በየ15 ቀኑ ቅዳሜ ቅዳሜ እየተገናኙ ልምዳቸው ይለዋወጣሉ። ውይይቱ ከመድኃኒት ጋር ያለ ችግር፣ ከቤተሰብ ጋር ያለ ተግዳሮት፣ በሥራ ቦታ ያለ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ተመሳሳይ የሕይወት ገጠመኝ ካላቸው ሰዎች፣ ተመሳሳይ የጤና እክል ከገጠማቸው ሰዎች ጋር ያለ መሸማቀቅ ይነጋገራሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቀድሞ ያለፈ ሰው ደግሞ ልምዱን ያጋራል። የገጠሙትን ተመሳሳይ ተግዳሮቶች አሸንፎ የወጣ የስኬት ታሪኩን ያካፍላል። መሸማቀቅ፣ ማፈር በሌለበት ሁኔታ ድክመቱን ለሌሎች ያጋራል። ድክመቱን ሳይነቅስ የሕይወት ልምዱን በማካፈል ለሌሎች ምርኩዝ ይሆናል። እሌኒ አንዳንድ ነገሮች ለሐኪም እና ለቤተሰብ መናገር ሊያስፈራ ይችላል፣ እዚህ ቦታ ግን ተመሳሳይ የጤና ተግዳሮት ላላቸው ሰዎች መናገር ትልቅ እረፍት ይሰጣል ትላለች። የአእምሮ ጤና ሕክምና ተጠቃሚዎች ዋነኛ ተግዳሮት በኅብረተሰቡ እና በቤተሰብ የሚደርስ መገለልና መድልዎ ነው የምትለው እሌኒ፣ ይህም ወደ ሆስፒታል ለመሄድ እክል መሆኑን ታዝባለች። ያለውን መገለልና መድልዎ ጥሶ ወደ እነርሱ ማኅበር የሚመጣ ሰው ቁጥርም አነስተኛ መሆኑንም አትሸሽግም።