በሂወትህ ደስታ ለማምጣት የሚያግዙ 4 ተግባሮች

ለብዙ ሰዎች ማንበብን እንደ ልማድ ለመያዝ አስቸጋሪ ነገር ነው። ምናልባት ለረዥም ሰዓታት ቁጭ ብሎ መጽሐፍት ማንበብ የሚችሉ ሰዎች የተለየ ችሎታ እንዳላቸው ሊታሰብ ይችላል። ነገር ግን እውነታው ሌላ ነው። አንድ ጊዜ የማንበብን ጥቅም የተገነዘበ ሰው በንባብ የሚያሳልፈው ጊዜ ላይታወቀው ይችላል።

ቢቢሲ በቅርቡ መጽሐፍ ማንበብን እንደ ህክምና መንገድ የሚጠቀሙ ባለሙያዎችን አነጋግሮ ነበር። ‘ቢብሊዮቴራፒስት’ የሚባሉት እነዚህ ባለሙያዎች ይህንን መንገድ በመጠቀም የተጨነቀ ሰውን ወደ ጤናማ የአእምሮ አሰራር መመለስ እንችላለን ይላሉ። በተለይ ደግሞ የልብ ወለድ መጽሐፍትን ማንበብ ዓለምን የምንመለከትበትን መነጽር እንድንቀይር እንደሚያደርግ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

በለንደን ስኩል ኦፍ ላይፍ ለሰዎች ግላዊ የንባብ ምክር የምትሰጠውና ቢብሎቴራፒስት የሆነችው ኤላ በርቱድ ለቀድሞዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን አይነት መጽሐፍ እንዲያነቡ እንደምትመክር ተጠይቃ ነበር። ”ቀላል ነው፤ አሜሪካዊው ጸሐፊ ሁበርት ሴልቢ በ1978 የጻፈውን ‘ሪኩዊየም ፎር ኤ ድሪም’ የተባለውን መጽሐፍ እመከራቸዋለው” ብላለች። ”በተለያየ አይነት የእጽ ሱስ ውስጥ ተዘፍቀው በሚገኙ አራት ሰዎች ህይወት ላይ ነው መጽሐፉ የሚያተኩረው። ዋና መልዕክቱም የህይወት ፍልስፍናችንን መቼም ቢሆን መልቀቅ እንደሌለብን ማሳየት ነው” ስትል ምክንያቷን አስቀምጣለች።

ሌላኛው ልብ ወለድ መጽሐፍት ሊያደርጉልን የሚችሉት ነገር፤ ታሪኩ ውስጥ የመግባት እድልን መፍጠር ነው። ለምሳሌ በቴሌቪዥን አንድ ፊልም ብንመለከት፤ ምስሉና ድምጹ በአንድ ላይ ስለሚቀርብልን ያለ ምንም ጥረት በቀላሉ መረዳት እንችላለን። ነገር ግን መጽሐፍ ሲሆን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው። በታሪኩ ውስጥ የምናገኛቸውን ገጸ ባህሪያት በምናባችን ለመሳል ነው የምንሞክረው። ይህ ደግሞ አእምሯችን የሚፈጠሩበትን ጥያቄዎች በሙሉ በራሱ እንዲመልሳቸው ያስችሉታል።

እጅግ ስለተዋበ ተፈጥሮአዊ ቦታ መጽሐፍ ላይ ስናነብ ሁሌም ቢሆን ጭንቅላታችን ውስጥ ትክክለኛውን ምስል ለማስቀመጥ እንሞክራለን። ታዋቂው ጸሀፊ አሌክስ ዊትል እንደሚለው በልጅነቱ እጅግ ከባድ ጊዜን አሳልፏል። በደቡባዊ ለንደን የልጆች ማሳደጊያ ውስጥ ነው ያደገው። ”በማደጎ ቤት ውስጥ ያጋጥሙኝ የነበሩትን አስፈሪና አስቸጋሪ ጊዜያት አሳልፋቸው የነበረው የምወዳቸውን ልብ ወለድ መጽሐፍት በማንበብና ያለሁበትን ዓለም በመርሳት በገጸ ባህሪያቱ ዓለም ውስጥ በመግባት ነበር” ይላል።

ያነበቡትን መጽሐፍ ደግሞ ማንበብን የመሰለ አስደሳች ነገር የለም ይላሉ ቢብሊዮቴራፒስቶች። ለመጀመሪያ ጊዜ ስናነበው የተሰሙን ስሜቶች፣ በድጋሚ ስናነበው በምናባችን የሳልናቸው ገጸ ባህሪያት ሁሉ ተቀይረው ልናገኛቸው እንችላለን። መጨረሻውን እያወቅን እንኳን ከመጨረሻው በፊት ያለውን መውደቅና መነሳት፣ ደስታና ሃዘንን ለማየት እንጓጓለን። አንዳንዴም የተረዳነው የመሰለን ሃሳብ በድጋሚ ስናነበው መሳሳታችንን ልናውቅ እንችላለን። ታዳጊ ህጻናት መጽሐፍ ማንበብ ሲጀምሩ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ እየተስተዋሉ የሚገኙትን የአእምሮ መታወክና ተያያዥ እክሎች ለማዳን አልያም ለመከላከል እጅጉን ይረዳቸዋል። ሁሌም ልጆች በዕለት ተዕለት ኑሯቸውና በአካባቢያቸው የሚገኙ የማይስማሟቸው እንዲሁም ምቾት የሚነሷቸው ሁኔታዎችን ለማምለጥ የራሳቸውን ዓለም ይፈጥራሉ። የሚፈጥሩት ዓለም ደግሞ ከመጽሐፍት ጋር የተገናኙ ከሆነ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።

መጽሐፍትን ማንበብ ለአእምሮ ጤና ይህን ያክል ጥቅም ካለው መጻፍስ?

አሌክስ ዊትል እንደሚለው በውስጣችን የሚሰሙንን ነገሮች በጽሑፍ ለመግለጽ መሞከር ጭንቀትን ለመቀነስ ይረዳል። የሚያሳስቡንን ነገሮች ለራሳችን ከማስቀረት ይልቅ በወረቀት ላይ ማስፈር ደግሞ ትልቅ ህክምና እንደሆነ ያምናል። በሌላ በኩል በርተን የተባለው ጸሐፊ ደግሞ ደራሲ መሆን ማለት ለሳምንታት፣ ለወራት አንዳንዴም ለዓመታት ከሰዎች ተነጥሎ መቆየትን ሊያስከትል እንደሚችል ያስባል። ነገር ግን ከእነዚያ ሁሉ ጭንቀትና መከራ በኋላ የተጻፈውን መጽሐፍ ሚሊዮኖች ሲያነቡትና ሲጠቀሙበት ማየትን የመሰለ አስደሳች ስሜት እንደሌለ ግን ሁሉም ጸሐፍት የሚስማሙበት ሃሳብ ነው።